2 Samuel 3

1በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ብዙ ጊዜ ቈየ፤ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ፣ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ መጣ።

2ዳዊት በኬብሮን ሳለ፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤

የበኵር ልጁ፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን፣
3ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ፣
ሦስተኛው፣ ተልማይ ከተባለው ከጌሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፣
4አራተኛው፣ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤
አምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣
5ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረኃም ነበር፤
እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው።

አበኔር ከዳዊት ጋር ተባበረ

6የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፣ አበኔር በሳኦል ቤት ላይ ኀይሉን ያጠናክር ነበር። 7ሳኦልም የኢዮሄልን ልጅ ሪጽፋን በቁባትነት አስቀምጧት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፣ “ለምንድን ነው ከአባቴ ቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው።

8አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ስለ ተቈጣ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለይሁዳ የምወግን የውሻ ጭንቅላት ነኝን? ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ ታማኝነቴን እስከ ዛሬ ድረስ አላጓደልሁም፤ አንተንም አሳልፌ ለዳዊት አልሰጠሁም፤ አሁን ግን አንተ ከዚህች ሴት ጋር በፈጸምሁት ነገር ትከሰኛለህን? 9እግዚአብሔር ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ እዳር እንዲደርስ ሳላደርግ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ክፉ ያድርግበት፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤ 10የማለለትም መንግሥትን ከሳኦል ቤት አውጥቶ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት የሰጠው ተስፋ ነው።” 11ኢያቡስቴም አበኔርን አጥብቆ ፈርቶት ስለ ነበር፣ እንደ ገና አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም።

12ከዚያም አበኔር ለዳዊት፣ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ተስማማ፤ እነሆ እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ እንዲመለስ እኔ እረዳሃለሁ” ብለው ለዳዊት እንዲነግሩለት መልክተኞች ላከ።

13ዳዊትም፣ “ይሁን እሺ፣ ከአንተ ጋር ስምምነቱን አደርጋለሁ፤ ነገር ግን ከአንተ አንዲት ነገር እሻለሁ፤ ይኸውም ወደ እኔ ስትመጣ በመጀመሪያ የሳኦልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ እንድትመጣ ነው፤ ያለዚያ ግን ወደ እኔ እንዳትመጣ” አለ። 14ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት።

15ስለዚህም ኢያቡስቴ መልክተኛ ልኮ፣ ሜልኮልን ከባሏ ከሌሳ ልጅ ከፈልጢኤል ወሰዳት። 16ባሏም እስከ ብራቂም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሏት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፣ “በል ይበቃል! ወደ ቤትህ ተመለስ” አለው። ስለዚህም ተመለሰ።

17አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ተመካከረ፤ እንዲህም አለ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ፈልጋችሁ ነበር፤ 18እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት።”

19እንዲሁም አበኔር ለብንያማውያን ራሱ ሄዶ ይህንኑ ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ። 20አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። 21ከዚያም አበኔር ዳዊትን፤ “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፣ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ሄጄ፣ ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።

ኢዮአብ አበኔርን ገደለው

22የዳዊትና የኢዮአብ ሰዎች በዚያኑ ጊዜ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለ ሄደ፣ በኬብሮን አልነበረም። 23ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፣ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መምጣቱን፣ ንጉሡ እንዳሰናበተውና እርሱም በሰላም እንደ ሄደ፣ ኢዮአብ ሰማ።

24ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምን ማድረግህ ነው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ እንዴት በሰላም እንዲሄድ አሰናበትኸው? 25የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፣ መውጣት መግባትህን ለማወቅና የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልል ነው።”

26ከዚያም ኢዮአብ ከዳዊት ዘንድ ወጣ፤ አበኔርን እንዲያመጡትም መልክተኞች ላከ፤ መልክተኞቹም ከሴይር የውሃ ጕድጓድ አጠገብ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር። 27አበኔር ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፣ ኢዮአብ በቈይታ የሚያነጋግረው በመምሰል ዞር አድርጎ ወደ ቅጽሩ በር ይዞት ሄደ፤ እዚያም የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ሲል፣ ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው።

28ዳዊት ይህን ነገር ቈይቶ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ንጹሕ ነን፤ 29ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም አሠቃቂ የቈዳ በሽታ
የዕብራይስጡ ቃል ማናቸውንም ዐይነት የቈዳ በሽታ የሚያመለክት ነው።
ያለበት፣ በምርኵዝ የሚሄድ ዐንካሳ፣ ወይም በሰይፍ ተመትቶ የሚወድቅ ወይም የሚበላው ያጣ ራብተኛ ከኢዮአብ ቤት አይታጣ።”

30አበኔር ገባዖን ላይ በተደረገው ጦርነት የኢዮአብንና የአቢሳን ወንድም አሣሄልን ገድሎት ስለ ነበር፣ እነርሱም አበኔርን ገደሉት።

31ከዚያም ዳዊት ለኢዮአብና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፣ “ልብሳችሁን ቀድዳችሁ፣ ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ራሱ ንጉሥ ዳዊትም አስከሬኑን አጀበ። 32ከዚያም አበኔርን በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ጮኾ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ።

33ንጉሡም ለአበኔር ይህን የሐዘን እንጕርጕሮ ተቀኘ፤

“አበኔር እንደ ተራ ሰው ይሙት?
34እጆችህ አልታሰሩም፤
እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤
ሰው በክፉ ሰዎች ፊት እንደሚወድቅ
አንተም እንደዚሁ ወደቅህ።”
ሕዝቡም ሁሉ እንደ ገና አለቀሱለት።

35ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እህል በሚቀምስበት ሰዓት ወደ ዳዊት መጥተው ምግብ እንዲበላ አጥብቀው ለመኑት። ዳዊት ግን፣ “ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ።

36ሕዝቡም ሁሉ ይህንኑ ተመለከቱ፤ ደስም አላቸው፤ በርግጥ ንጉሡ ያደረገው ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው። 37እንዲሁም በዚያን ዕለት ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንዳልገባበት ዐወቁ። 38ከዚያም ንጉሡ ለራሱ ሰዎች እንዲህ አለ፤ “በዛሬዪቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን? 39ምንም እንኳ ዛሬ የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም፣ እኔ ደካማ ሰው ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ ልጆች እጅግ በርትተውብኛል። እግዚአብሔር ለክፉ አድራጊ የእጁን ይስጠው።”

Copyright information for AmhNASV